Skip to main content
im2

ህፃናትን ከተለያዩ በሽታዎች በመታደግ፣ ጤናቸው እንዲሻሻልና ሞት እንዲቀንስ ከፍተኛ እገዛ ከሚያደርጉ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ውስጥ ግንባር ቀደም የሆነው የህፃናት አድን ድርጅት/ Save The Children / የጤና መረጃ ስርዓትን ለማቀላጠፍ የሚያግዙ ኮምፒውተሮች፣ፕሪንተሮችና ታብሌቶችን ለሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ በዛሬው ዕለት አስረክቧል። የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ሰላማዊት መንገሻ ድጋፉን በተረከቡበት ወቅት እንደተናገሩት የህፃናት አድን ድርጅት/ Save The Children / ለቢሮው ትርጉም ያለውና ወቅቱን የጠበቀ እገዛ በማድረጋቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው ድርጅቱ ከቢሮው ጋር ተቀራርቦ በመስራቱ በተለይም የህፃናት ጤናን ለማሻሻል ብሎም ሞት ለማስቀረት በተሰራው ስራ በክልሉ ይበል የሚያስብል ውጤት መጥቷል ብለዋል። የክትባት አገልግሎት ጥራትን ለማረጋገጥ ድርጅቱ በክልሉ 3 ወረዳዎች ላይ እያደረገ ያለው ድጋፍ ከፍተኛ ነው ያሉት ሀላፊዋ መረጃን በተገቢው በማደራጀትና በመጠቀም ረገድ የሚስተዋሉ ጉድለቶችን ለመቅረፍ አጋዥ የሆኑ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ድጋፍ በማድረጋቸው በቢሮው ስም ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።። ሀላፊዋ አክለውም ሀገራዊ አቅጣጫን በተከተለ መልኩ በክልሉ ከማህበረሰብ ጀምሮ በየደረጃው ባሉ የጤና ተቋማት የተሰበሰቡ መረጃዎችን ወጥና የዘመነ ለማድረግና በአንድ ላይ በማቀናጀት ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን አስታውሰው በዛሬው ዕለት በድጋፍ የተገኙት ቁሳቁሶች የክትባት አገልግሎቱን ብቻ ሳይሆን ሌሎች የጤና ፕሮግራሞችንም ጭምር ለማጠናከር የላቀ አበርክቶ እንዳላቸው ጠቁመው ፣ የሚረከቡ ወረዳዎችም የመረጃ ጥራት ላይ ሞዴል ወረዳ ለመሆን እንዲሰሩ አሳስበዋል። የህጻናት አድን ድርጅት /Save The Children/ ደቡባዊ ቀጠና ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሀይሉ ተስፋዬ በበኩላቸው በሲዳማ ክልል የክትባት አገልግሎት ጥራትን ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎች በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስታውሰው በዛሬው ዕለትም ድርጅታቸው 14 ዴስክቶፕ ኮንፒተሮች፣ 9 ፕሪንተሮች እንዲሁም 25 ታብሌቶች በአጠቃላይ ከ2.4 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ማቴሪያሎች ድጋፍ በማድረግ መረጃዎች ወጥና ዘመናዊ እንዲሆኑ በማድረግና በማዘመን የህፃናት ጤና በሚፈለገው ልክ እንዲሻሻል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል። በህጻናት አድን ድርጅት /Save The Children/ የክትባት ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት ወ/ሮ ምዕራፍ ሰለሞን በበኩላቸው የህጻናት አድን ድርጅት /Save The Children/ እንደ ሀገር በጤናና በሌሎች የልማት ፕሮግራሞች ላይ እየሰራ መሆኑን፣ በተለይም የክትባት ተደራሽነትን በማስፋት፣ከ5 አመት በታች ባሉ ህፃናት ላይ የሚከሰተውን ሞት ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ህፃናት በተወለዱ አንድ አመት ውስጥ ምንም አይነት ክትባት ያላገኙ / ዜሮ ዶዝ / እና ክትባት ጀምረው ያቋረጡ ህፃናትን ለይቶ ወደ አገልግሎቱ ለማምጣት፣ ከቤት ለቤት ጀምሮ በየጊዜው የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ በማድረግ የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከር ይገባል ሲሉ በአፅንኦት ተናግረዋል። የሲዳማ ክልል መንግስት ጤና ቢሮ ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች ይመልከቱ Website: https://www.shb.gov.et Facebook: https://www.facebook.com/share/1EUdJhqmFM/ https://www.facebook.com/1000649355740¡57/posts/1065870482254128/ Telegram : https://t.me/SidamaRHB Twitter: https://x.com/sidama_health_bureau WhatsApp: https://chat.whatsapp.com/K7W4vwM1mqG8SyGz4PYC71 YouTube: https://youtube.com/@sidamahealthbureau?si=bjGP9rGIpwIlZWQX Tik Tok: https://vm.tiktok.com/ZMBCWXXxa/